Sun, Sep 08
|Sankofa Video, Books & Cafe
Book Event - "Be-Ente Ethiopia" Book Launch, and Discussion
Join us 6pm Sunday, September 8th, for Wondimu Geda's new Amharic book"Be-ente Ethiopia", followed by a discussion!
Time & Location
Sep 08, 2024, 6:00 PM – 8:00 PM
Sankofa Video, Books & Cafe, 2714 Georgia Ave NW, Washington, DC 20001, USA
About The Event
ስለ 'በእንተ ኢትዮጵያ' ከወንድሙ ገዳ
‘በእንተ* ኢትዮጵያ’ ብዬ በሰየምኩት በዚህ መጽሐፍ በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያን ፖሊቲካዊ፣ ማህባራዊና ባህላዊ ሁኔታዎች በተመለከተ በተሰሙኝ ስሜቶችና በታዩኝን እውነታዎች መሰረትነት እነዚኽኑ ለመዳሰስ፤ ለማኄሳ፤ ለመጠየቅና ለመሞገት ተሞክሯል፡፡ አንደኛው የጽሑፉ ግብ የውይይት መነሻሀሳቦችንና ጥየቄዎችን ለአንባብያን፣ ለሕዝቡና ጉዳዮቹ በተለይ ለሚመለከቷቸው አካላት ማቅረብ ነው፡፡ በሀገራችን እየደረሱ ላሉ ውስብስብ ችግሮች በየዘመኑ የተፈራረቁ መንግስታት ዋነኛ የኃላፊነት ድርሻ እንደተጠበቀ ሆኖ ለገባንበት የተግዳሮት አዙሪት ተጠያቂው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ተጨባጭ መፍትሄውም (ጣት ከመጠቋቆም፣ እልህ ከመጋባትና ከመበሻሸቅ
ባሻገር) የእያንዳንዱ ዜጋ የድርሻውን ማዋጣትና ተግባራዊ ሀላፊነቱን መወጣት ነው የሚለው ዋነኛ የመጽሐፉ ማጠንጠኛ ሀሳብ ነው፡፡ ከጥንት እስከአሁን ያሉና የነበሩ የፖለቲካ መሪዎቻችንም ሆኑ ምሁራን ለጥፋት በለው ልማት ከሌላ አለም የተላኩብን ባእድ ፍጡራን ሳይሆኑ የባህሎቻችንና የፍልስፋናዎቻችን ውልደቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም የጽሑፍ አንዱ መነሻ ሀሳብ አምባገነን መንግስታት ብቻቸውን ይህንን የተግዳሮት አዙሪት ሊያስቀጥሉ አይችሉም የሚል ነው፡፡ ‘እንንቃና ለመፍትሄዎች እንሰባሰብ፤ ባለአፍሮ አይገባ መስቀል ቄስ፣ የነገር ውል አራቂ ወልይ፣ ግጭት ፈቺ አበጋር፣ አዋቂ አስታራቂ አባቦኩ፣ ልበብር እመምኔት፣ የበቁ ሸሆይ፣ ጉምቱው ቃዲ፣ የነቃሽ ዱበርቲ፣ የተምታቱ አስተሳሰቦችን አጥርታችሁ የምታቀርቡልን አራት አይና ንኡዳን፣ ጉልሃን ምሁራን ሆይ፣ እነሆልን እኛና እዳችን! ውሎ ካደረ አጥቦ ለማፅዳት የማይቻል፣ ደንጋራ (መላየለሽ) የበቀል ዘር በየቦታው እየበቀለ ነውና ተቤዡን፡፡ ‘ገሃነማውያን በንፍር ውሃ ነደዱ’ እንደተባለው፣ እዚሁ የሚልጥ የሚለመጥጥ የጸብ እንግርጋቦት ፈጀን፡፡ ሀገራችን ተጣብቆ የሚቆረቁር የሚያስፎክታትን ቆዳ ገፈው-ከልተው-ሸልተው የሚያነሱላት ሁነኛ ሰዎች ያስፈልጓታልና ተቤዡን፡፡ ተቤዡን፤ የህማማተ መስቀላችንን ፍጻሜ አፍጥኑልን! ተቤዡን፤ አብሮን ከዘመን ዘመን ተሻጋሪውን መጠላለፍ
ለአንዴና ለመመጨረሻ ጊዜ በጥበብ ጋዲ ጠልፋችሁ ጣሉልን፡፡ ተቤዡን!’ የሚል ጥሪ ለማቅረብ የሞከርኩበት ጽሁፍ ነው፡፡
በመጽሐፍ አይነኬ አይወሬ የተባሉ አንዳንድ ጎጂ የመሰሉኝን ባህሎቻችንንና አስተሳሰቦቻችንን ነቅሶ በማውጣት በምክንያት ለመሞገት ተሞክሯል፡፡ የጋራ መዋጮ ውጤት ያልሆነ ምንም ነገር የለም፤ አውቀንም ይሁን ባለማወቅ እያንዳንዳችን ለጥፋት ቤት ሥራ ያቀበልነው/ያዋጣነው የአድልዎ፣ ሙስና፣ ዘረኝነትና ጸብ ጡብ ቀለም፣ ርዝመት፣ ውፍረትና ቅጥነት ነው ቢለያይ፡፡ እናም ግለሰቦችና የተወሰኑ ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ ህዝብም ይገመገማል፤ ይተቻል የሚል አቋም አንጸባርቄያለሁ፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን የውይይት መነሻ ሀሳቦች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ለባዶ፣ እመኀበ አልቦ ምኞቶቻችን ስንገብርና በሀሳብ ስንቃትት የምንኖር መሆን የለበትም፤ ትልማችንንና ጥረታችንን ሁሉ ሾተላይ እንደተጻረረው ሊቀር አይገባም፡፡ ‘በእንተ ኢትዮጵያ’ “የኢትዮጵያ ህዳሴ ቅዳሴው እንደታጎለ እንዳይቀር፣ የተግዳሮት አዙሪቱ እንዲያበቃ በመጀመሪያ ወደየራሳችን እንመልከት፡፡ ኑ ሀገራችንን እንታደጋት፡፡ ኑ ትብታቡን እንፍታ! ኑ ኢትዮጵያዊነት እንደገና ያቆጥቁጥ፡፡ የሁሉም ነገር መነሻ፣ ማስፈጸሚያና ፍጻሜ ፍቅር ነውና ኑ ለፍቅር፣ ለእውነተኛ እኩልነት፣ ለሰላምና እድገት እንክተት! ኑ!” የሚል ሀገራዊ ጥሪ የቀረበበት ጽሑፍ ነው፡፡
*በእንተ-ስለ
ከወንድሙ ገዳ
ወንድሙ ገዳ እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት ሰኔ 15፣ 1963 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ደቡብ ምእራብ ሸዋ፣ ከሚሳ በምትባል የገጠር አካባቢ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የምኖረው በአሜሪካ ሃገር፣ ዋሽንግተን ዲሲ ነው፡፡ የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የተማርኩት ከሚሳ፣ ወላይታ ሶዶና ጂማ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በወላይታ ሶዶ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቀቅኹ፡፡ ቀጥሎም በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በእንግሊዘኛ ቋንቋና ስነጽሑፍ በዲፕሎማ ተመርቄያለሁ፡፡ ከምረቃ በኋላ በተለያዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሳስተምር ቆይቼ አዲስአበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት ለመጀመሪያ ዲግሪ የእንግሊዘኛ ቋንቋና ስነጽሑፍ ያጠናሁ ሲሆን፣ ቆይቶም ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዘኛ ስነጽሑፍ ሁለተኛ ዲግሪ አግኝቼያለሁ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ በነበርሁበት ወቅት የትርፍ ሰዓት ጋዜጠኛ በመሆን በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አገልግዬያለሁ፡፡
በጎንደር ዩኒቨርስቲ በእንግሊዘኛ ቋንቋና ስነጽሑፍ ትምህርት ክፍል በመምህርነትና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ በመሆን ሰርቼያለሁ፡፡ ከ2001 ዓ.ም. ወደ አሜሪካ እስከመጣሁበት 2004 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚና በዩኒቨርስቲው የድኅረምረቃ መርሃግብር ክፍል ተቀጥሬ የሠራሁ ሲሆን፣ በዚሁ ዩኒቨርስቲም አስተምሬያለሁ፡፡
ከጽሑፍ በተያያዘ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ አጭርና ረጅም ልብወለዶችንና ግጥሞችን ስጽፍ የቆየሁ ሲሆን በ2016 ዓ.ም. ‘አሌፍ ቤት’ የተባለውን የልብወለድ ሥራ አሳትሜያለሁ፡፡ ክብር ሽልማት ባዘጋጀው ውድድር ‘አሌፍ ቤት’ ከዓመቱ ምርጥ አምስት ረጅም ልብወለዶች አንዱ ሆኖ የተመረጠ መጽሐፍ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ‘በእንተ* ኢትዮጵያ’ በሚል ርእስ አዲስ መጽሐፍ ጽፌያለሁ፡፡
*በእንተ-ስለ